10ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም በሰመራ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት መካሄድ ጀመረ።

 

የከተማ ልማትን ከብሔራዊ የልህቀት ራዕይ ጋር በማስተሳሰር ቀጣይነት ባለው መልኩ ለመምራት ያለመው 10ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ዛሬ ቅዳሜ በአፋር ክልል ዋና ከተማ በሆነችው ሰመራ ስታዲየም በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ተከፈተ።

መድረኩ “የከተሞች ዕድገት ለኢትዮጵያ ልህቀት” በሚል ታላቅ መሪ ሀሳብ ስር የሚመራ ሲሆን፣ ከመላው ኢትዮጵያ ከ150 በላይ ከተሞች የሚወክሉ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ከተለያዩ ተቋማት የመጡ እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል።

የፎረሙ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት የፌዴራልና የክልል መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከናውኗል።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ አደም ፋራህ፣የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ክቡር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒን ጨምሮ፣ሌሎች የክልልና የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች በመድረኩ ተገኝተዋል።

ይህ የከተሞች መድረክ ለቀጣዮቹ አምስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን፣ የከተማ አገልግሎት አሰጣጥን ጥራት ማሻሻል፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ፈተናዎችን መፍታት፣ እንዲሁም በተለያዩ የከተማ ልማት ዘርፎች የላቀ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ከተሞችን ልምድ መለዋወጥ ላይ ሰፊ ትኩረት እንደሚሰጥ ይጠበቃል።